የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ተሰማርተው እንዲያለሙና ለልማታችን እድገት ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክቱ የሚያደርግ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የግል ባለሀብቶች ወደ ዞናችን ገብተው እንዲያለሙ ለማስቻል፤ ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት በመከተል፣ የኢንቨስትመንት መሬት አዘጋጅቶ በመስጠት፣ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ፣ባዛርና ኤግዚቢሽን በየዓመቱ በማዘጋጀት የዞኑን የኢንቨስትመንት አቅምን በማስተዋወቅ፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጭ ዕድሎችን በተለያዩ አማራጮች በማስተዋወቅ ሌሎችም ዘርፉን የሚመለከቱ በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በተደረገው ጥረትም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ዞናችን የሚመጣው የባለሀብት ፍሰት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ የተፈጠረውን ሀገራዊ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመን እንቅስቃሴ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ በዞናችን በግል ባለሀብቱ የልማት ተሳትፎ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡

ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ በኢንድስትሪ ዘርፍ 191፣ በግብርና ዘርፍ 54 እና በአገልግሎት ዘርፍ 59 በአጠቃላይ 304 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 3,004,986,313 (ሶስት ቢሊዮን አራት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ስድስት ሺህ ሦስት መቶ አስራ ሶስት ብር) ካፒታል ያስመዘገቡ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደዉ እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ለ2303 ዜጎች በቋሚ እና 2,431 በጊዜያዊ በድምሩ ለ4,734 ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ ውስጥ 2014 በጀት አመት በዞኑ በምደባ እና በልዩ ጨረታ በኢንድስቱሪ 16፣ በግብርና 4 እና በአገልግሎት ዘርፍ 14 በአጠቃላይ 34የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማዉጣት ያስመዘገቡት ካፒታል በኢንዱስቱሪ 464,157,893 ብር፣በግብርና 69,921,931ብር በአገልግሎት 1,069,223,105 ብር በድምሩ 1,603,302,929 ብር ካፒታል ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
አዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶች ለ1,670 ቋሚ እና ለ1,228 ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩ አስመዝግበዋል፡፡በአጠቃላይ በቅርብ አመታት የዞኑን የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጭ እድሎች እና ፖቴንሻል የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ይህንንም ተከትሎ የዞኑ ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለዚህም አብነት ማሳያ የሚሆን በ2014 በጀት አመት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች 492 በላይ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች በሁሉም መዋቅር መቅረቡ በቂ ማሳያ ነዉ፡፡